ዜና ዜና

Back

“በተከፈለው መስዋዕትነት በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ስርዓት እውን ሆኗል”

ታጋይ ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚኬኤል

29ኛው የትግራይ ሰማዕታት ቀን ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ የአዲስ አበባና አከባቢዋ የህወሓት ታጋዮች ማሕበር ቅርንጫፍ አስተባባሪነት በታላቅ ድምቀት ተከበረ፡፡ በዝግጁት ላይ የተገኙት ታጋይ ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል እለቱ የተለየ መሆኑን በመግለፅ በተከፈለው መስዋዕትነት አምባገነኑን የደርግ ስርዓት በመቀየር በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ ወደ ትግል የገባው ወዶ አልነበረም ያሉት ታጋይ ዶ/ር ድብረፅዮን የደርግ መንግስት ሁሉንም አማራጮች የዘጋ አምባገነን በመሆኑ እንኳንስ የብሄር መብት ማክበር ይቅርና በግልም ጭምር ማሰብን የማይፈቅድ አስከፊ ስርዓት ሰለነበረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም በተከፈለው ከባድ መስዋዕትነት ያንን አስከፊ ስርዓት መቀየር ተችሏል ብለዋል፡፡

ደርግ ባለፈበት ሁሉ ቤቶችን እያቃጠለ፣ በተደጋጋሚ በአየር እየደበደበ ከዚያም ከፍ ሲል  በሓውዜን ምድር ላይ ማንም በራሱ ዜጋ ላይ ያደረገዋል ብሎ የማይገመትን ግፍ በዚህች ታሪካዊ ቀን ሰኔ 15 በራሱ መንግስት በገበያ ላይ በጠራራ ፀሀይ ህዝብ ጨፍጭፏል ሲሉ ያስታወሱት ዶ/ር ደብረፅዮን ዛሬ በተከፈለው ሁሉን አቀፍ መስዋእትነት በመላው ሀገሪቱ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ስርዓት እውን ሆናል ብለዋል፡፡

በሰማእታት መስዋእትነት የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ መብት ተከብሯል፣ የጤና ሽፋን እያደገ መጥቷል፣ ትምህርት ለሁሉም ዜጋ ተዳርሷል፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ረገድም አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል፤ መንግስትም በጠብመንጃ ሳይሆን በህዝብ ይሁንታ ወደ ስልጣን የሚመጣበት ስርዓት እውን ሆኗል ብለዋል ዶ/ር ደብረፅዮን፡፡

በመጨረሻም ታጋይ ዶ/ር ደብረፅዮን ተጋግዘንና ተባብረን ወደፊት መራመድ ይገባናል በማለት ስርዓቱን ከጸረ ሰላም ሃይሎች በመጠበቅና ጠላቶቻችንን ከመቃብር በታች በማስገባት የሰማዕታትን አደራ መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ በሕይወት ያሉትን ታጋዮች ማክበር፣ ማጋዝ ከዚህ ትውልድ ይጠበቃል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡


መግለጫ መግለጫ