ዜና ዜና

Back

የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር በተለዩ ጉዳዮች ተጨማሪ ውይይት በማካሄድ ቅድመ ድርድር ሂደትን አጠናቀቁ

የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለፈው ሳምንት ለድርድር በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ ተጨማሪ ውይይት በማካሄድ የቅድመ ድርድር ሂደቱን ባለፈው ቅዳሜ አጠናቅቀዋል፡፡ ድርድር እንዲካሄድባቸው ከቀረቡ አጀንዳዎች መካከል በአብዛኛዎቹ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ድርድር እንዲካሄድባቸው ስምምነት ከተደረሰባቸው አጀንዳዎች በተጨማሪ በአስቸኳይ የጊዜ አዋጅ  አለም አቀፍ የድንበር እና የባህር በር፤ የመሬት ፖሊሲ፣ የህገ መንግስት መሻሻል እንዲሁም የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች የሚሉ አጀንዳዎች ድርድር እንዲደረግባቸው የድርድሩ ተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠይቀዋል፡፡

የኢህአዴግ ተወካይ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አስቸኳይ የጊዜ አዋጁ አሁን በትግበራ ላይ የሚገኝ በመሆኑ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የድንበር ጉዳይ ስራው በሚመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚከናወን መሆኑን በመግለጽ ድርድር እንዳማይካሄድባቸው ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካና የህሊና እስረኛ የሚባል እንደሌለ በመግለጽ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ይሁን አይሁን ህግን ተላልፎ  በህግ ቁጥጥር የዋለ ሰው የፖለቲካና የህሊና እስረኛ ሊባል አይችልም ብለዋል፡፡ ‹‹አለአግባብ የታሰረ ማንኛውም ሰው ካለ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ሊጠበቅለት ስለሚገባ ማቅረብ ትችላላችሁ፤ ካልሆነ ግን የህግ የበላይነት  ለድርድር መቅረብ የለበትም›› ብለዋል፡፡

 የመሬት ፖሊሲ ለድርድር የሚቀርብ አለመሆኑ እና በአፈጻጸም ዙርያ ግን መደራደርና መወያየት እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡

እንደ አቶ ሽፈራው ገለጻ ህገ መንግስት የሚሻሻለው  በህገ መንግስታዊ አሰራር እንጂ በድርድር ባለመሆኑ ለድርድር መቅረብ አይገባውም፡፡

ፓርቲዎቹየ ብሄራዊ መግባባት፣ የዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ እና አደረጃጀት፣ የዜጎች በየትኛውም ቦታ ተዘዋውሮ የመስራት መብት ጋር የሚነሱ ጉዳዮችና ከመሬት ጋር በተያያዘም የዜጎች መፈናቀልና የካሳ ስርዓት እንዲሁም የሊዝ አዋጅ ዙሪያ፣ በምርጫ ህጎች፣ የጸረ ሽብር አዋጅ፤ መገናኛ ብዙኃን አዋጅ፤ የታክስ፣ ንግድ፣ ኢንቨስተምንት፣ የፋይናንስ አዋጅ፣ የፍትህ አካላት አደረጃጀት አዋጅ፣ የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅ በሚሉ አጀንዳዎች ለመደራደር ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

የድርድሩ መሪዎች የድርድር አጀንዳዎች ቅደም ተከተልና የድርድሩ አጠቃላይ ማዕቀፍ የጊዜ ሰሌዳ አዘጋጅቶ እንዲያዘጋጁና በፍጥነት ወደ ድርድሩ እንዲገቡ በመስማማት  ውሏቸው ቋጭተዋል፡፡

 

 

 

 

 


መግለጫ መግለጫ