ዜና ዜና

Back

የፌዴራል መንግስት የ2010 በጀት 320 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ሆኖ ፀደቀ

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል መንግስት የ2010 በጀት 320 ቢሊዮን 803 ሚሊዮን 602 ሺ 160 ብር  በጀቱ  በምክር ቤት አባላቱና በህዝብ አስተያየት መስጫ መድረኮች ተመከሮበትና አስፈላጊውን ሂደት አልፎ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡ በጀቱ ከ2009 በጀት ከነበረው 274 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር በዘጠኝ ነጥብ ስድስት በመቶ ብልጫ አለው፡፡

ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ድረስ ተግባራዊ የሚደረገው በጀት ለመደበኛ ወጪዎች 81 ቢሊዮን 839 ሚሊዮን 528 ሺ 570 ብር፤ 114 ቢሊዮን 703 ሚሊዮን 641 ሺ 453 ብር ደግሞ ለካፒታል ወጪዎች እንደሚውል ተገልጿል፡፡

በ2ኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትኩረት ለተሰጣቸው የትምህርት፣ የመንገድ፣ የግብርና፣ የውሃና የተፈጥሮ ሃብት፣ የጤና እና የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራሞች ከአጠቃላይ በጀት ውስጥ 61 ነጥብ 8 በመቶ ያህሉ የተመደበ ሲሆን 7 ቢሊዮን ብሩ ደግሞ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ እንዲውል ተመድቧል።

ከጠቅላላ በጀቱ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ለክልሎች የሚደረግ ድጎማ ሲሆን 117 ቢሊዮን 260 ሚሊዮን 432 ሺህ 137 ብር በጀት መያዙ ተጠቁሟል፡፡ 7 ቢሊዮን ብር ለዘላቂ ልማት ግቦች ማሳኪያ የተያዘ ሲሆን የወጣቶች የተዘዋዋዋሪ ፈንድ፣ የከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ዘርፎችም በበጀቱ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል ይገኙበታል።  

የፌደራል መንግስትን የካፒታል ወጪዎች ለመሸፈን የታቀደው ከሀገር ውስጥ ከሚሰበሰብ ገቢና ከውጭ ሀገር በሚገኝ እርዳታና ብድር መሆኑ ታውቋል።

 

 


መግለጫ መግለጫ