Web Content Display Web Content Display

የግንቦት 20 የብር ኢዮቤልዩ በዓል ማጠናቀቂያ በአዲስ አበባ ስታዲየም በድምቀት ተከበረ

በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ፕሮግራሞች ሲከበር የቆየው የግንቦት 20 የብር ኢዮቤልዪ በዓል ማጠናቀቂያ በኢዲስ አበባ ስታዲየም ሲከበር የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባ ዱላ ገመዳ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ያለው አባተና የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሁም በርካታ የድርጅትና የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በመታደም ደማቅ የበዓል አከባበር ተደርጓል፡፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ የማርች ባንዶችና የራስ ቴያትር የሙዚቃ ቡድን በመገኘት ለበዓሉ ድምቀት ሆነው ተሳታፊዎችን ሲያዝናኑ ቆይተዋል፡፡ በተጨማሪም የበዓሉ ተሳታፊዎች በተለያዩ አደረጃጀቶች በመሆን በዓሉን የተመለከቱ ሙዚቃዎችን በማዜም በዓሉ ተጨማሪ ድምቀት እንዲኖረው አድርገዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በዓሉን በንግግር የከፈቱ ሲሆን ግንቦት 20 አምባገነኑና ጨቋኙ የደርግ ስርዓት የተገረሰሰበት ብቻ ሳይሆን ስር የሰደደ የድክነትና የድንቁርና ምዕራፍ ተዘግቶ ሀገራችን ወደ ብልፅግናና ህዳሴ ጉዞ የጀመረችበት አዲስ ምዕራፍ ነው ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ አዲስ አበባ ባለፉት 25 ዓመታት ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጦችን በማስመዝገብ በህዳሴ ጉዞ ላይ መሆኗንና በርካታ ተስፋ ሰጪ የግንቦት 20 ፍሬዎችን በማፍራት በቀጣይ ጥረቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡ ለዚህም መላ ህብረተሰቡ ተለመደውን የልማትና ሰላም ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የጭቆናና የአፈና ስርዓት ተገርስሶ የህዳሴ ጉዞ ለተጀመረበት የግንቦት 20 ቀን እንኳን በሰላም አደረሳችሁ በማለት በዓሉን የተመለከተ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ እያከበርን ያለነው የግንቦት 20 የብር ኢዮቤልዩ በዓል የሚከበርበት ምክንያት በዋናነት ደርግን ለመጣል የተደረገው ትግል እልህ አስጨራሽ የነበረውን ያህል በቀጣይ ድህነት ከሀገራችን ለማጥፋት የሚደረገው ትግል እንዲሁ ጠንካራ እንደሚሆን መግባባት የምንፈጥርበት መሆኑን ለማመላከት ጭምር ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

በቀድሞዋ ኢትዮጵያ ዜጎች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የማያደርጉባትና ቢያደርጉም በጠራራ ፀሃይ የሚገደሉት የነበረች መሆኗን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስሩ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ እናቶች ልጅ ወልደው ለማሳደግ የማይሳቀቁባት፣ ሁሉም ዜጎች በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ያለገደብ ተሳትፎ የሚያደርጉባትና እንዲያደርጉም የምትጠይቅ ሆናለች ብለዋል፡፡ ሀገራችን በከፍተኛ የእድገት ለውጥ ውስጥ ስትሆን ለውጡ በውስን የሀገሪቱ አካባቢዎች ወይም ከተሞች ብቻ ታጥሮ የቀረ ሳይሆን በሁሉም ሀገሪቱ ማዕዘናት ከከተማ እስከ ገጠር የዘለቀ ለውጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአጠቃላይ ሀገራችን በቀጣይ የጀመረችን ዘርፈ ብዙ የእድገት ለውጥ አጠናክራ ለማስቀጠል የሰው ሀብት ልማቱ ወደር የማይገኝለት አለኝታ በመሆኑ ይህንኑ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባና የዚሁ ተግባር ዋነኛ ባለቤት የሆኑት መምህራን ደከመንና ሰለቸን ሳይሉ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን መንግስትም የመምህራንን የአቅም ግንባታና የኑሮ ሁኔታ ማለትም የመኖሪያ ቤት፣ የትራንስፖርትና የደመወዝ ሁኔታ ለማሻሻል የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የስርዓቱ አደጋ የሆኑትን አክራሪነትና አሸባሪነትን በፅኑ መታገል እንደሚገባና በቀጣይ ድርጅታቸው ኢህአዴግና መንግስታቸው ለሚያከናውኑት የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ መላው ህብረተሰብ ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ በዓሉ በሌሎች ሌዩ ልዩ ፕሮግራሞች ቀጥሉ በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

News News

የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ መደበኛ ጉባኤ አመራሮችን በመምረጥ ተጠናቀቀ

“በወጣቶች የላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የህዳሴ ጉዞአችንን እናፋጥናለን” በሚል መሪ ቃል ከግንቦት 17 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤ ዴሞክራሲያዊ በሆነ አካሄድ ሊጉን እስከቀጣይ ጉባኤ ድረስ የሚመሩ አመራሮችን በመምረጥ ተጠናቀቀ፡፡ ወጣት ሙቀት ታረቀኝ በሰብሳቢነት የተመረጠ ሲሆን ወጣት አክሊሉ ታደሰ በምክትልነት ሊጉን እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡“በወጣቶች የላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የህዳሴ ጉዞአችንን እናፋጥናለን” በሚል መሪ ቃል ከግንቦት 17 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ሶስተኛ መደበኛ ጉባኤ ዴሞክራሲያዊ በሆነ አካሄድ ሊጉን እስከቀጣይ ጉባኤ ድረስ የሚመሩ አመራሮችን በመምረጥ ተጠናቀቀ፡፡ ወጣት ሙቀት ታረቀኝ በሰብሳቢነት የተመረጠ ሲሆን ወጣት አክሊሉ ታደሰ በምክትልነት ሊጉን እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡

“ወጣቶች የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብን ለመድፈቅ ቆርጠው መነሳት አለባቸው” የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ

“ከ25 ዓመታት በፊት የነበሩ ወጣቶች ራሳቸውን አቅልጠው ለእኛ ብርሃን ሆነዋል” ያሉት አቶ ኃይለማርያም ወጣቶች የግንቦት ሃያ ትሩፋቶችን ጠብቆ ይበልጥ ወደፊት ለመገስገስ ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ወጣቶች ጎራ ሳያደበላልቁ ጎራቸውን ለይተው በጽናት ተፋልመው የደርግን ስርዓት ማስወገዳቸውን አስታውሰው አሁንም ወቅቱ የሚጠይቀውን ትግል ለማድረግ የጎራ መደበላለቅ ሳይኖር በጽናት መታገል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

“በግንቦት ሃያ ድል ሰላሟ፣ አንድነቷና ክብሯ የተጠበቀ አገር ፈጥረናል” አቶ አባይ ጸሓዬ

ኢህአዴግ አገር ማስተዳደር ሲጀምር ኢኮኖሚው በከፍተኛ ድቀት ላይ እንደነበር አስታውሰው በመጀመርያ አስር አመታት የ5 ነጥብ 5፣ ባለፉት 12 ዓመታት ደግሞ ከ10 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ በአማካይ የ8 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡ እንደ አቶ አባይ ገለጻ ኢትዮጵያ ሰላሟ፣ አንድነቷና ክብሯ የተጠበቀና በብዙ መስኮች ለሌሎች አርአያ መሆን የምትችል አገር ሆናለች፡፡

የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ 3ኛ መደበኛ ጉባኤ የሊጉ አመራርና የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን በመምረጥ ተጠናቀቀ

በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ተገኝተው ለጉበኤያተኛው መልዕክት ያስተላለፉት የጠቅላይ ሚንስትሩ የአደረጃጀት አማካሪ ሚንስትርና የኢህአዴግ ም/ቤት ጽ/ቤት ኃላፊ ጓድ ከበደ ጫኔ በደርግ ላይ በተካሄደው ትግል ኢህአዴግን ለድል ያበቃው ለሴቶች፤ ለአርሶ አደሮች፤ ለወጣቶችና ለሌሎች ማህበራዊ መሰረቶች ያለው ውግንና መሆኑን ጠቅሰው አደረጃጀቶች የማህበራዊ መሰረቶቹን ጥቅም ለማረጋገጥ ግንባር ቀደም ሆነው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

portrait of Meles portrait of Meles

Quick Links Quick Links

25 ዓመት የግንቦት 20 የብር ኢዮቤልዩ በዓልን አስመልክቶ ከኢህአዴግ ም/ቤት ፅ/ቤት የተሰጠ መግለጫ

ህዝባዊነታችንን ጠብቀን የአገራችንን የህዳሴ ጉዞ እናፋጥን!

 

የተከበራችሁ መላ የአገራችን ህዝቦች

ሃያ አምስተኛው የግንቦት 20 የብር ኢዮቤልዩ በዓል ባለፉት የትግልና የድል አመታት ባካሄዳችሁት እልህ አስጨራሽ ትግልና በከፈላችሁት መስዋዕትነት አምባገነናዊ ስርአት ተወግዶ፤ አገራችንን ከጥፋት አፋፍ ላይ አድርሷት የነበረው የዘመናት የማሽቆልቆል ጉዞ ተቀልብሶ በምትኩ የህዳሴና የከፍታ ጉዞ እንድትጀምር ያስቻላት በመሆኑ ታላቅና ታሪካዊ ብሄራዊ በዓላችን ነው፡፡ በዓሉን ስናከብር በሩብ ምእተ አመት ጉዟችን ያገኘናቸውን ድሎች አጠናክረን ለማስቀጠልና የሚያጋጥሙ ችግሮችንና ፈተናዎችን በተለመደው ህዝባዊ ጽናት እየታገልን በማለፍ የህዳሴ ግስጋሴያችንን ለማስቀጠል በመዘጋጀት ነው፡፡

ያለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የአገራችን ህዝቦች በድርጅታችን ኢህአዴግ መሪነት በየወቅቱ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በፅናት በመታገል፣ በተሳካ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ እያለፉ በርካታ አኩሪ ድሎችን ያስመዘገቡበት ዓመታት ነበሩ፡፡ በሩብ አመቱ ጉዟችን ሊጠናከሩና ሊሰፉ የሚገባቸው በርካታ ድሎችን የተጎናጸፍንበት ከመሆኑ ባሻገር  ለቀጣዩ የአገራችን የህዳሴ ጉዞ ጠቃሚ ልምዶችና ትምህርቶች ያገኘንበት በመሆኑ የበዓሉን ፋይዳ ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ የተጓዘችበት የሩብ ምዕተ ዓመት ጉዞ ለዘመናት ያለፍንበት የማሽቆልቆል ሂደት ተገትቶ በሁሉም መስኮች ወደፊት የተራመድንበት ነበር፡፡ አገራችን የአዲሱን ሥርዓት ግንባታ የጀመረችው ከምንም ነገር በፊት የዴሞክራሲ መብቶች ያለገደብ የሚከበሩበት ሁኔታ በመፍጠር ነበር፡፡ ለዘመናት በማሽቆልቆል ጉዞ ውስጥ የኖረችው አገራችን ከማንኛውም ዓይነት ውድቀት ነፃ ልትወጣ የምትችለው የዜጎቿና የህዝቦቿ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲከበሩ ብቻ መሆኑ ታምኖበት መሠረተ ሰፊ የዴሞክራሲ ስርአት መገንባት የተጀመረው የደርግ ሥርዓት ከወደቀባት ከመጀመሪያዋ ዕለት ጀምሮ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት መጀመሪያ በሽግግሩ ቻርተር፣ ቀጥሎም በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት በመመራት የተካሄደው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ የግለሰብና የቡድን መብቶች ተደጋግፈው እንዲከበሩ አስችሏል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገነባው ዴሞክራሲያዊ ስርአት መሠረተ ሰፊ ብቻ ሳይሆን፣ ህጋዊ ዋስትና የተረጋገጠበት ይሆን ዘንድ፣ ህዝቡ ቀጥተኛና ወሳኝ ሚና በተጫወተበት አኳኋን ህገ-መንግስታችን ጥልቅ ዴሞክራሲያዊ ባህርይ ተላብሶ እንዲቀረፅ ተደርጓል፡፡ አገራችን በምትመራበት ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟሉ የዴሞክራሲ መርሆዎች የህገ-መንግስታችን የማዕዘን ድንጋይ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ህገመንግስታዊ እውቅናና ጥበቃ ተደርጎላቸዋል፡፡ የብሔርና ብሔረሰብ፣ የሃይማኖትና የፆታ እኩልነት መብቶች ተከብረዋል፡፡ በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ለመሆን በቅተዋል፡፡ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስታችንን በመከተል በተካሄደው ጥረት አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ከኖረችበት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ በመላቀቅ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ልትያያዝ በቅታለች፡፡

የዴሞክራሲያዊ ስርአታችን አሁንም በለጋ እድሜ ላይ የሚገኝና ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በአገራችን ለዘመናት ስር ሰደው ከቆዩት የጸረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዞች ታሪካዊ ሁኔታ እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰባቸው አገሮች ልምድ አኳያ ሲታይ በሩብ ምእተ አመት ጉዟችን የተመዘገቡ ስኬቶች ስርአቱ የደረሰበትን የጥንካሬ ደረጃ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችን የተመዘገቡ ስኬቶች ከስርአቱ ተፃራሪ የነበሩ አስተሳሰቦችን ለማሸነፍ ዴሞክራሲያዊና ህዝባዊ ትግል በማድረግ የተገኙ የአገራችን ህዝቦች የትግል ውጤቶች ናቸው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በህዝብ ነፃ ምርጫ ብቻ የሚያዝ እንዲሆን በየምርጫው የተደቀኑ ፈተናዎችን በፅናት ታግሎ በማለፍ በየአምስት አመቱ ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብቶችን ተግባራዊ ለማድረግ በብዝሃነት ላይ የተመሰረተውን ፌዴራላዊ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ህዝባዊ ትግል ተካሂዷል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

ያሳለፍነው የሩብ ምዕተ አመት ጉዞ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ መስኮችም ስር-ነቀልና መሰረታዊ ለውጦች የመጡበት ነበር፡፡ በሃያ አምስት ዓመታት ጉዟችን ኢኮኖሚያችን ለዘመናት ከኖረበት የማሽቆልቆል ጉዞ ወጥቶ ፈጣንና ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ በማድረግ ላይ የሚገኝ ዕድገት የተመዘገበበት ነው፡፡ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በአማካይ በየዓመቱ ከ8 በመቶ በላይ አገራዊ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ በተለይ ከተሃድሶ መጀመር በኋላ ባሉት 14 ዓመታት ደግሞ በአማካይ ከ10 በመቶ በላይ ዓመታዊ ዕድገት የተመዘገበ መሆኑ በእርግጥም አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቀውን የማሽቆልቆል ጉዞ ምእራፍ በአስተማማኝ ደረጃ ተዘግቶ ቀጣይነት ያለው የዕድገት ጎዳና የተያያዘች መሆኑን ያሳያል፡፡ የተከተልነው ትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫ ኢትዮጵያ የፈጣን ብቻ ሳይሆን ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ፍትሃዊነት ያለው እድገት ማስመዝገብ የቻለች አገር መሆኗ የተረጋገጠበት ነው፡፡ በአገራችን የተመዘገበው እድገት በሁሉም የኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች የተመዘገበ ከመሆኑ ባሻገር ከገጠር እስከ ከተማ ሁሉንም አካባቢዎችንና የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረገና በማድረግ ላይ የሚገኝ ሁሉን አቀፍና መሰረተ ሰፊ ነው፡፡ 

በገጠር አርሶ አደሩ ከመሬት ሳይነቀል ምርታማነቱን እንዲያሳድግና እንዲጠቀም በተከፈተው ዕድልና በተሰራው ዘርፈ ብዙ ስራ ለዘመናት በድህነት የኖሩት የአገራችን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ምርታማነታቸውና ገቢያቸው እንዲሻሻል ተድርጓል፡፡ በከተሞችም የአነስተኛና ጥቃቅን፣ የማኑፋክቸሪንግና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲስፋፋ መደረጉና በዚህም ሰፊ የህዝብ ተጠቃሚነት መረጋገጥ መጀመሩ በእርግጥም አገራችን ፈጣን ብቻ ሣይሆን ፍትሃዊ ዕድገት እያመጣች መጓዟን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በድርጅታችን የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት ልማት መስፋፋት በሰጠው ትኩረት በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች ለዕድገት ቁልፍ የሆነ የመሠረተልማት አገልግሎት መስፋፋት እንዲጀምር አስችሏል፡፡ ከትንሿ የጫራ ጫራ ግድብ ተነስቶ አስከ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የዘለቀው የኢነርጂ ልማት፣ ቀበሌን ከቀበሌ ከሚያገናኙ የገጠር መንገዶች እስከ ረዣዥም የባቡር መንገዶችና ደረጃቸውን የጠበቁ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ፣ ከትንሿ ምንጭ ማጎልበት እስከ ትላልቅ የመጠጥና የመስኖ ግንባታ የተስፋፋው የውሃ ልማት፣ ከአናሎግ ወደ ዲጂታልና ፋይበር ኬብሎች የተሸጋገረው የቴሌኮም አውታር ዝርጋታና የመሳሰሉት አገራችን ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት ሁነኛ አቅሞች በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡

በማህበራዊ ልማት መስክ ትምህርትን ለማስፋፋት በተደረገው ጥረት ከአገሪቱ ህዝብ መካከል 30 በመቶ ያህሉ ከአጸደ ህጻናት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባሉት ደረጃዎች በመደበኛ ትምህርት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ27 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ያሏት አገራችን አነስተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ያላቸውን ሃያ አምስት የአፍሪካ አገሮች ድምር የህዝብ ብዛት ያህል የሰው ኃይል በማስተማር ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ትልቅ ውጤት አገራችን ትምህርት የልማት ውጤትና የልማት መሳሪያ ብቻ ሳይሆን፣ የህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጫ እንዲሆን በማመን ያደረገችው አኩሪ እንቅስቃሴ ውጤት ነው፡፡ በጤና መስክ በተለይ ደግሞ መከላከልን ማዕከል ያደረገ የጤና አገልግሎት በማስፋፋት የተካሄደው እንቅስቃሴ በአገራችን ጤናው የተጠበቀ ህብረተሰብ ለመገንባት አስችሎናል፡፡ የጤና ተቋማትንና የጤና ባለሙያዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ ከፍተኛ ስኬት ተመዝግቧል፡፡ ባለፉት አመታት ህዝቡን በማሳተፍ በተካሄዱ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ቀደም ሲል የዜጎቻችንን ህይወት እንደ ቅጠል ሲያረግፉ የነበሩ እንደ ወባ ያሉ ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል የበርካታ ዜጎቻችንን ህይወት መታደግ ተችሏል፡፡ የእናቶችንና የህጻናትን ሞት በመቀነስ የተገኘው ውጤትም አበረታችና ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ነው፡፡

ምንም እንኳ በማህበራዊና አኮኖሚያዊ ልማት መስክ  የህዝባችንን ችግሮች ሙሉ በሙሉ ያልተቀረፉና ጥረቱን አጠናክረን መቀጠል የሚገባን መሆኑ ባያጠያይቅም፣ አገራችን በፈጣን የዕድገት ጎዳና መረማመዷ በተጨባጭ የማሽቆልቆል ምዕራፍ የተዘጋበትና ትክክለኛ የህዳሴ አቅጣጫ እንደተከተለች የሚያሳይና የተከተልናቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት በአገራችን በየወቅቱ በተከሰቱ የድርቅ አደጋዎች ምክንያት በርካታ ዜጎቻችንን ህይወታቸው ሲቀጠፍ እንደነበር  የሚታወስ ነው፡፡ ካለፈው አመት ጀምሮ እስከ ያዝነው አመት የዘለቀው ከአለም የአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዞ የተከሰተው ድርቅ አገራችን በታሪኳ ካጋጠሟት የድርቅ አደጋዎች ከፍተኛው የሆነና የ10.2 ሚሊዮን ዜጎቻችን የእለት እርዳታ ፈላጊዎች እንዲሆኑ የዳረጋቸው ቢሆንም በዋነኛነት  ባለፉት 25 አመታት የድል ጉዟችን በፈጠርነው አገራዊ የልማት አቅም ድርቁ ወደ ረሃብነት ሳይቀየር የዜጎቻችንን ህይወት መታደግ መቻሉ የወርቃማ ድሎቻችን አንዱ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በአጠቃላይ አሁንም ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ ድርቅ፣ የመኖሪያ ቤት እና የመሳሰሉትን ችግሮች የመፍታት ስራ ደርጅታችን አጽንኦት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይም አጠናክሮ የሚቀጥልበት የትኩረት ማእከሉ ይሆናል፡፡  

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት አገራችን ከተጎናፀፈቻቸው ከፍተኛ የትግል ትሩፋቶች መካከል ሌላው ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም የሰፈነባት አገር መሆኗ ነው፡፡ ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ በማያባሩ የእርስ በእርስ ግጭቶች ብዙ ዋጋ የከፈለችው አገራችን፣ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የአስተማማኝ ሠላም ባለቤት ልትሆን ችላለች፡፡ ውስጣዊ ችግሮቿን በዴሞክራሲ መሳሪያነት ለመፍታት የተንቀሳቀሰችው አገራችን የዜጎችንና የህዝቧን መብት አክብራ ለመጓዝ በመቻሏ የአስተማማኝ ሠላም ባለቤት ለመሆን ችላለች፡፡ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ለሰላሳ ዓመታት ያህል ባልተቋረጠ ጦርነት የተጠበሰችውና "ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር" በሚል መፈክር ትታወቅ የነበረችው አገራችን፣ እነሆ ባለፉት ዓመታት መላ ትኩረቷን በዴሞክራሲ፣ ሠላምና ልማት ላይ አድርጋ ወደፊት እየተራመደች ትገኛለች፡፡ "ከድህነትና ኋለቀርነት በላይ ጠላት የለንም" በማለት መላ የአገራችን ህዝቦች የሚያካሄዱት አኩሪ ትግል ውስጣዊ ሰላማችንን ዘላቂና በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባ አድርጓታል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ የራሷን ውስጣዊ ሠላም ለማረጋገጥ የቻለችባቸው እነዚህ ዓመታት ለአፍሪካ ሠላም መጠናከር ልዩ አስተዋፅኦ ያደረገችባቸው ዓመታትም ነበሩ፡፡ ከቡሩንዲ እስከ ሩዋንዳ፣ ከላይቤሪያ እስከ ሶማሊያ፣ ከዳርፉር እስከ ደቡብ ሱዳን በዘለቀ ውጤታማ የሠላም ማስከበር ተሳትፎ ከራሷ አልፋ የአፍሪካውያንን ሠላም ያስከበረች አገር መሆኗን አስመስክራለች፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ጎረቤቶቿ ሁሉ የሚተማመኑባት የሠላምና የመልካም ጉርብትና ምንጭም ሆናለች፡፡

መላ የአገራችን ህዝቦች ባካሄዱት አኩሪ ትግል ኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የለውጥና የዕድገት አገር መሆን ጀምራለች፡፡ ይህን ተከትሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረው የጦርነትና ረሃብተኛነት ምስሏ በፍጥነት መቀየር ጀምሯል፡፡ በጦርነትና በረሃብ ተምሳሌነት ትገለፅ የነበረችው ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ የፈጣን ዕድገት አብነት ሆናለች፡፡ በፈጣን የዕድገት ታሪካቸው በእስያ ነብርነት እንደተሰየሙት የምስራቅ እስያ አገሮች ሁሉ ፈጣን ዕድገታችንን ተከትሎ ኢትዮጵያም በአፍሪካ አንበሳነት መታወቅ ጀምራለች፡፡ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ በቅርብ የሚከታተሉ አፍሪካውያን ወንድምና እህቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ የኢትዮጵያን ዕድገት በጥርጣሬ ይመለከቱ የነበሩ የገበያ አክራሪ ኃይሎች ጭምር የሚቀበሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በአገራችን እውን የሆነው መልካም ነገር ሁሉ በአንድ በኩል ድርጅታችን በህዝብ አጋልጋይነት መንፈስ እየተመራ አገራችንን በፍጥነት ለመለወጥ በቀየሳችው ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ለመመራት በመቻላችን፣ በሌላ በኩል ደግሞ መላ የአገራችን ህዝቦች ከዳር እስከዳር ለለውጥ ተነሳስተው በቁርጠኝነትና በተደራጀ ንቅናቄ በመንቀሳቀሳቸው የተገኘ ውጤት ነው፡፡ ከድርጅታችን ትክክለኛ አቅጣጫና ከህዝባችን አኩሪ ትግል ውጭ በአገራችን የማሽቆልቆል ምዕራፍ ተዘግቶ አስተማማኝ የዕድገት ምዕራፍ ሊከፈት እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ በየምዕራፉ ያጋጠመንን ፈተናዎችና እንቅፋቶች ሁሉ በህዝባዊ ፅናትና በብስለት እየመከትን ለአኩሪ ውጤት ልንበቃ የቻልነው በእርግጥም ህዝባችንን ይዘን አገራችንን በመልካም ጎዳና ለመምራት ባካሄድነው የተሳካ ትግል ነው፡፡

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በሁሉም የህይወት መስኮች ለውጥ እያመጣን በተጓዝንበት ሂደት የተጎናፀፍናቸው ድሎች ለጀመርነው ረጅሙ የአገራችን የህዳሴ ጉዞ መሰረት የሚሆን ጅምር ለውጥ እንደሆነ ድርጅታችን በጥብቅ ይገነዘባል፡፡ በተጨማሪም ይህን የለውጥ ሂደት ሊያደናቅፉ የሚችሉ ፈተናዎች ያልተለዩበት የለውጥ ሂደት እንደነበረም ይቀበላል፡፡ ትላንት ከትላንት ወዲያ የነበሩት የሥርዓቱ ፈተናዎች በትግል ከተፈቱ በኋላ በመንገዳችን ላይ አዳዲስ ፈተናዎች እየተጋረጡ እንደሆነና እነዚህንም በተለመደው ፅናትና ህዝባዊ ወገንተኝነት መፈታት እንዳለባቸው ይገነዘባል፡፡ የግንቦት 20 የብር ኢዩቤልዩ በዓልን በምናከብርበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት እያጋጠሙን የሚገኙ ችግሮችንና ፈተናዎችን በመፍታት ለቀጣይ ድል ለመዘጋጀት ቃል ኪዳናችን የምናድስበት መሆኑን ድርጅታችን በጽኑ ያምናል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

ድርጅታችን ኢህአዴግ  የትግል መስመሩን ባጠራበት የተሃድሶ እንቅስቃሴው በአገራችን ለዘመናት ስር ሰዶ የቆየው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችን ዋነኛ ፈተና መሆኑን አንጥሮ በማስቀመጥ፣ ባለፉት አመታት በአንድ በኩል የልማታዊ አስተሳሰብና ተግባርን በማጎልበት በሌላ በኩል የኪራይ ሰብሳቢነትን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ለማዳከም የሚያስችሉ ትግሎች የተካሄዱ ቢሆንም አሁንም ኪራይ ሰብሳቢነት የስርአታችን ዋነኛ ፈተና እንደሆነ ይገኛል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት በሚል ስያሜ የሚታወቀው በመንግስትና በህዝብ ሃብትና ፀጋ ህጋዊ አስተዋፅኦ ከሚፈቅደው በላይ ካለአግባብ የመጠቀም አመለካከትና ተግባር አሁንም የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችንን እየተፈታተነው ይገኛል፡፡ ይህ ችግር በኢኮኖሚ መስክ ካለአግባብ በመጠቀም ብቻ ሳይወሰን ለመልካም አስተዳደር እጦትና በዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ላይ ችግር እያስከተለ እንደሚገኝ በመገንዘብ በ10ኛው ድርጀታዊ ጉባኤያችን ምልአተ ህዝቡን ያሳተፈ ትግል ማካሄድ እንደሚገባን አቅጣጫ መቀመጡ የሚታወስ ነው፡፡ በጉባኤያችን አቅጣጫ መሰረት የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ የሚገኙ ቢሆንም አሁንም መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የቀጣይ ትግል የሚጠይቅ ሆኖ ይገኛል፡፡

ድርጅታችን ኢህአዴግ የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባር በቁርጠኝነት የመታገል ጉዳይ የተጀመረውን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ የለውጥ ሂደት ከሚያጋጥመው አደጋ የመጠበቅ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ያምናል፡፡ ከኢትዮጵያ ህዝቦች መብት፣ ተጠቃሚነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት በላይ ምንም ፍላጎት ለሌለው ድርጅታችን፣ ህዝብን ያስመረሩ ድክመቶች ይታረሙ ዘንድ ራሱን የማጥራትና የማብቃት ስራ አጠናክሮ የሚቀጥልበት መሆኑን ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል፡፡ ይህ ኢህአዴግና ሥርዓቱን ከማንኛውም ጉድፍ የማፅዳት ጉዳይ ደግሞ ከህዝቡ ተሳትፎና ትግል ውጭ ሊሳካ እንደማይችልም ድርጅታችን  በፅኑ ያምናል፡፡ በመሆኑም የግንቦት ሃያን የብር ኢዩቤልዩ በአል በምናከብርበት በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ምልአተ ህዝቡ በአገራችን በመካሄድ ላይ ያለውን የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግና ለችግሮቻችን ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ ለማስገኘት የጀመረውን ተሳትፎና ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች

አገራችን የማሽቆልቆል ጉዟዋ ተገቶ የከፍታ ጉዞ ላስጀመራት ታላቅ ድል ለመብቃት የቻለችው በርካታ ልጆቿ በከፈሉት ክብር መስዋእትነት በመሆኑ ድሉን አጠናክሮ የማስቀጠል ጉዳይ ከሁሉም ዜጎቿ የሚጠበቅ አደራ ነው፡፡ ዛሬም እንደትላንቱ ሁሉ አገራችንን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ ላይ የማድረስ ጉዳይም ከፈተናዎች የፀዳ ሆኖ ሊካሄድ የማይችል መሆኑን ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ ህዝባዊ ድሎቻችን የሚጎለብቱትና የሚጠናከሩት በየመድረኩ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በፅናትና በብስለት በማለፍና ለውጤት በማብቃት መሆኑ ካለፈው የትግልና የድል ጉዟችን በትምህርትነት የሚወሰድ ዋነኛ ቁም ነገር መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡

የግንቦት ሃያን የብር ኢዩቤልዩ በአል በምናከብርበት በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ በሥርዓታችን ፊት የተደቀኑ ፈተናዎችን ከህዝባችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን እንደምንፈታቸውና አገራችን የ50ኛውን አመት የወርቅ ኢዩቤልዩ የድል በዓሏን ስታከብር ወደ ከፍተኛ ገቢና የበለጸገ ህብረተሰብ ለመሸጋገር አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደምትደርስ በመተማመን ነው፡፡

ይህ የአገራችን ሩቅ አላሚ ራእይ ሊሳካ የሚችለው ሁሉም የአገራችን የህብረተሰብ ክፍሎች እጅ ለእጅ ተያይዘው የድርሻቸውን መወጣት ሲችሉ መሆኑ ካለፈው የትግልና የድል ጉዟችን የምንገነዘበው መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑ የገጠሩም ሆነ የከተማው የአገራችን ምልአተ ህዝብ በተደራጀ ንቅናቄ በልማትና በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታው ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ድርጅታችን በዚህ ታሪካዊ የድል በአል ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ሁሉም የአገራችን ዜጎች በተሰማራችሁበት መስክ ሁሉ በትጋት በመስራትና የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ አኩሪ ድል ለማስመዝገብ ርብርብ በማድረግ በድህነት ላይ የጀመርነውን ዘመቻ በድል ለማጠናቀቅ የሚጠበቅባችሁን አገራዊ ተልእኮ እንድትወጡ ደርጅታችን ጥሪ ያቀርብላችኋል፡፡ የአገራችን ሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶቻችሁን በማጠናከር ተሳትፏችሁንና ተጠቃሚነታችሁን በማስፋት የአገራችንን የህዳሴ ጉዞ በማፋጠን ተልእኳችሁን አጠናክራችሁ እንድትወጡ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ድርጅታችን አንግቦ የተነሳውን ህዝባዊ አላማ ከዳር ለማድረስ መላ የድርጅታችን አባላት ህዝባዊ ወገንተኛነታችሁንና የአላማ ጽናታችሁን በመጠበቅ በሁሉም መስኮች የግንባር ቀደም ሚናችሁን በተለይ ደግሞ እራስን ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በማጽዳት ሌሎችን በመታገል የግንባር ቀደም ሚናችሁን ከምንጊዜውም በላይ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ድርጅታችሁ ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

የህዳሴ ጉዟችን በስኬታማነት ይቀጥል ዘንድ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን የማስፈጸም አቅም መጠናከር እንደሚገባው ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ ባለፉት 25 አመታት ሲቪል ሰርቪሱ ቀድሞ ከነበረበት የገዥዎች አገልጋይነት ወደ ህዝባዊ አገልግሎት ሰጭነት ለማሸጋገር በርካታ ስራዎች የተሰሩ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ከሚፈለገው ደረጃ ላይ ያልደረሰና በተለይ ህዝባችንን ለቅሬታ የዳረጉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በስፋት የሚታዩበት ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር የመንግስት ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች የተጀመረውን የሪፎርምና የለውጥ ስራ አጠናክሮ በማስቀጠል፣ የህዝብ አገልጋይነት አመለካከትና ብቃት በማጎልበት የሚጠበቅባችሁን ተልእኮ በብቃት እንድትወጡ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በአገራችን በተፈጠረው ከፍተኛ የትምህርት እድል በሁሉም ደረጃዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎቻችን የትምህርት እድል ተጠቃሚ መሆናቸውንና በዚህ ረገድ መምህራን እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ መምህራን የህዳሴ ጉዟችንን ከግብ ማድረስ የሚችል ሁለንተናዊ ብቃት ያለው የሰው ኃይል በማፍራት ትውልድን በአግባቡ የመቅረጽ ከባድ ተልእኳችሁን አጠናክራችሁ እንድትወጡ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስታዊ ስርአታችን ለዜጎቻችን ካጎናጸፈው መሰረታዊ መብቶች ውስጥ ፍትህ የማግኘት መብትና ለዚሁ መብት ተግባራዊነት የዳኝነት ነጻነት የተረጋገጠ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከ25 አመት በፊት ለአብዛኛው የአገራችን ህዝብ እንደ ሰማይ ርቆ ይታይ የነበረው ፍትህ የማግኘት መብትን በማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች የተመዘገቡ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም በፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ህዝባችን በህገ መንግስቱ የተጎናጸፈውን መብት በተሟላ ሁኔታ እንዳያገኝ እንቅፋት እየፈጠረበት እንደሚገኝ ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ ስለሆነም የፍትህ ተቋማት የተጀመረውን ሪፎርም በማጠናከር የዜጎችን ህጋዊ መብቶች በማስከበር በህገ መንግስቱ የተሰጣችሁን ከባድ ኃላፊነት በብቃት እንድትወጡ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ባለፉት የትግልና የድል አመታት የአገራችን የጸጥታ ኃይሎች የውጭ ወረራን በመመከት፣ የሽብር ድርጊቶችን ጨምሮ የጸረ ሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴዎችን በማክሸፍና በመከላከል እንዲሁም በሌሎች አገሮች የሰላም ማስከበር ተግባር በመሳተፍ ስኬቶችንና ድሎችን በማስመዝገብ የአገራችን ህዝብ የተረጋጋና ሰላማዊ ህይወት እንዲኖር ህዝባዊ ተልዕኳችሁን በብቃት እየተወጣችሁ መሆኑን ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡ አሁንም "በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል" እንዲሉ የአገራችንን እድገትና ለውጥ በበጎ የማይመለከቱ የውጭና የአገር ውስጥ የጸረ ሰላም ሃይሎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሰላማችንን ለማደፍረስ ከመሞከር ወደኋላ እንደማይሉ በመገንዘብ ህዝባዊ ተልእኳችሁን አጠናክራችሁ እንድትወጡ ድርጅታችን በዚህ አጋጣሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በምንከተለው በነጻ ገበያ መርህ የሚመራ ልማታዊና ዴሞክራሲያው ስርአት ግንባታ የግል ባለሃብቶች ሚና ከፍተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዛሬ 25 አመታት በፊት በአገራችን ከ500ሺ ብር በላይ ኃብት ማፍራት ከማይፈቀድበት የእዝ ኢኮኖሚ በመላቀቅ በአገራችን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ከፍተኛ ኃብት ያፈሩ በርካታ ባለሃብቶች ተፈጥረዋል፡፡ በአገራችን እየተመዘገበ ላለው እድገትም የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ የአገራችን ባለሃብቶች ለዚህ ስኬት የበቁት ግንቦት 20 ባጎናጸፋቸው ድልና እየተገነባ በሚገኘው የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርአት አማካኝነት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም የአገራችን ባለሃብቶች የስርአቱ አደጋ ከሆነው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር እራሳችሁን በማጽዳት ባላችሁ ብቃት አማካኝነት በጤናማ የገበያ ውድድር መርህ በመመራትና በመወዳዳር በልማታዊ አቅጣጫ እራሳችሁን እና አገራችሁን በመጥቀም በአገራችን የህዳሴ ጉዞ ተልእኳችሁን አጠናክራችሁ እንድትወጡ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡

በውጭ አገር የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊን በአገራችን በሚካሄደው ሁለንተናዊ ለውጥ ተሳትፏችሁን በማጠናከር እራሳችሁን፣ ቤተሰቦቻችሁንና አገራችሁን በመጥቀም የድርሻችሁን እንድትወጡ ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ህገ መንግስቱ ያጎናጸፋቸውን መብት ተጠቅመው በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው  በነጻነት  በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ የፖለቲካ አቋም ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆኖ ድርጅታችን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በሚያግባቡ መሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት የወሰደውን ግልጽ አቋም አጠናክሮ የሚቀጥልበት ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤቶች በማጠናከር ድርጅታችን የበኩሉን ድርሻ አጠናክሮ ለመወጣት የተዘጋጀ መሆኑን በድጋሚ እያረጋገጠ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህግንና ሰለማዊ የትግል አቅጣጫን በመከተል በአገራችን የህዳሴ ጉዞ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በመጨረሻም ባለፉት 25 አመታት የተጎናጸፍናቸውን ወርቃማ ድሎቻችንን ጠብቀን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን በመድፈቅ የአጋራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ በድርጅት፣ በመንግስትና በህዝብ አቅሞች የተደራጀ የልማት ሰራዊት ግንባታ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን ህዳሴያችንን እናፋጥን፡፡

"በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለህዳሴያችን"

"ዘላለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት"

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ኢህአዴግ የንድፈ ሃሳብ መፅሔት የሆነችው አዲስ ራዕይ የመጋቢት - ሚያዚያ ዕትም ለአንባቢዎቿ እየቀረበች ነው፡፡ መፅሔቷ ሁለት ርዕሰ ጉዳዮችን በመያዝ ለህትመት የበቃች ሲሆን  እርስዎም እንደተለመደው መፅሔቷን ገዝቶ በማንበብ ግንዛቤዎን ያሳድጉ፡፡ መልካም ንባብ!